Skip to main content
0001

የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ነው፦ አቶ ገብሬ ጋጌ

የካቲት 6/2018 ዓ.ም

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥና የአገልግሎት አሰጣጦችን ለማቀላጠፍ በልዩ ቅንጅትና ትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ያዘጋጀው፣ ለክልሉ ተቋማት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች  ፎካል ፈጻሚዎችና ለዞንና ልዩ ወረዳ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪዎች ግምገማ ነክ የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

መድረኩን ያስጀመሩት የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ ፣በክልሉ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥና አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ በተደረጉ ርብርቦች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ 2018 በጀት ዓመት በዕቅድ የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በተደረገው ጥረት በመጀመሪያዉ ግማሽ ዓመት የዕቅዱን 91.6 ከመቶ ማሳካት መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ህዝብን ማገልገል ታላቅ ክብር መሆኑን ያስታወቁት አቶ ገብሬ፣ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ማጉላላት፣ማመናጨቅ እና ጉቦ መጠየቅ የመሳሰሉ ችግሮች እንዳሉ በምስላ ተገልጋይ ጥናት እና በተደረጉ ድጋፋዊ ክትትሎች  መለየታቸውንም ገልጸዋል።

 የተቋማት የዕቅደቸዉ የመጀመሪያ ግብ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለይቶ መፍታት ነው ያሉት ቢሮ ሃላፊው፣የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በአግባቡ ላይቶ የመፍታት ጉዳይ በክልሉ መንግስት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጣው አስታውቀዋል።

ማገልገል ትልቅ ክብር መሆኑን መገንዘብ፣የመናበብና የመንጠባጠብ ችግሮችን መፍታት፣አገልግሎትን ማዘመንና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ቁልፍ ተግባራት ስለመሆናቸውም አቶ ገብሬ ጋጌ አሳስበዋል።

የተለምዶ አሰራር መቅረት እንዳለበት በመድረኩ ያሳሰቡት ሃላፊው፣የክልሉ መንግስት ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲደርስና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ በ17 ከተሞች የሞሶብ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተረባረበ ይገኛል ብለዋል።

ክልሉ ያሉትን ዕምቅ አቅሞች አቀናጅቶ በማልማት ሞዴል ክልል ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ገብሬ፣እነዚህ ጥረቶች ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን ዕምነት የሚያሳድሩ ስለመሆናቸውም አመላክተዋል።

ህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት የማግኘት መብት አለው፣ ተቋማት ደግሞ ፈጣን አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸውም ያሳሰቡት ቢሮ ሃላፊው፤የተሻለ አሰራርና የሰመረ ውጤት ለማምጣት መረባረብ ተገቢ መሆኑንም አሳውቀዋል።

የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የመልካም አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ይስሐቅ ቢጃሞ በበኩላቸው የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን በመተግበር ክልላዊ ዕቅዶችንና አገራዊ ህልሞችን ማሳካት ይገባል ብለዋል።

በክልሉ መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ይስሐቅ፣መድረኩ ጥንካሬዎችን ለይቶ ለማስፋትና ጉድለቶችን ለማረም የታለመ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በዘርፉ የሚታዩ የወጥነት ችግሮችን ተቀናጅቶ ማረም፣መልካም አስተዳደር መርሆዎችን ከማስተገበር አኳያ ያሉ ውስንነቶችን ማስተካከል እና ክልሉ በሁሉም ዘርፎች ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲወጣ መረባረብ ተገቢ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ሃላፊው አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የተለያዩ ተቋማት ያካሄዷቸውን ጥናቶችና ነባራዊ ሁኔታዎች የተመለከቱ ጽሁፎች ቀርበዉ ዉይይት ተደርጓል፡፡ በመድረኩ የቢሮው ምክትል ሃላፊዎች፣የማናጅመንት አባላት፣የክልል ተቋማት የመልካም አስተዳደር ፎካል ፈጻሚዎችና  የዞንና ከልዩ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያና የጽ/ቤት ኃላፊዎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።