Skip to main content
zena9

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበራዊ ክላስተር ተቋማት አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀንን "ሙስናን ለመዋጋት ወጣቱን ባለቤት ማድረግ፤ ነገን መገንባት!" በሚል መሪ ቃል በወራቤ ከተማ ተከብሯል። በዚሁ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የሀገርን እድገት የሚያቀጭጭ በመሆኑ በቅንጅትና በትብብር መከላከል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ከአገልግሎት አሰጣጥና በሀገር ልማት ስራዎች ጋር ተያይዘው የሚፈፀሙ የሙስና ተግባራት ደግሞ የሀገርን እድገት የሚያቀጭጩ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል። ችግሩን በተቀናጀ መልኩ ለመግታት በዘርፉ የወጡ ህጎችን በአግባቡ በመተግበር ተጠያቂነትን ማስፈንና መከላከሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የክልሉ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ታየች ሞላ ሙስናን መከላከል በአንድ ተቋም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል። የክልሉ ምክትል ኮሚሽነር ፈሲጋ ጌታቸው በክልሉ ሙስናን ለመከላከል በርከታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል። እንደ ምክትል ኮሚሽነሮቹ ገለፃ ሙስና መልኩ ብዙ መሆኑን ተከትሎ ተግባሩን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀው ለውጤታማነቱ ሁሉም ማገዝ እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።