"የህዘብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የፐብሊክ ሰርቪስ የሪፎርም ስራዎችን በሙሉ አቅም መተግበርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ይገባል" የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ። (ሆስዕና፣ ታህሳስ 8/2017) የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በክልሉ በየደረጃው ከሚገኙል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች እና ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር በሪፎርምና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ በቡታጅራ ከተማ መክሯል። በመድረኩ ምክር ቤቶች አስፈጻሚ አካላትን ከመገምገም አንጻር ያላቸው ሚና፤ የመልካም አስተዳደር መርሆች እና የህዝብ ክንፍ አሰራርን በተመለከተ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ መድረኩን በመሩበት ወቅት የህዘብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የፐብሊክ ሰርቪስ የሪፎርም ስራዎችን በሙሉ አቅም መተግበርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል። በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች የሪፎርም ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አፈ-ጉባኤዎች እና ቋሚ ኮሚቴዎች የክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መመሪያ ስጥተዋል። የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት፤ የፐብሊክ ሰርቪስ የሪፎርም ስራዎች ላይ አቅም በፈቀደ ደረጃ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በቀጣይ ይጠናከራል። አቶ ገብሬ የፐብሊክ ሰርቪስ የሪፎርም ስራዎች በክልሉ ውጤታማ እንዲሆኑ ተቋማቸው ተቀናጅቶ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት አረጋግጠዋል። የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በቀጣይ ሚናቸውን መወጣት የሚያስችለውን ግብዓት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ የሪፎርም ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።