ስለ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ቢሮ
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ ሲቪል ሰርቪስ በጥቅምት 14/1900 ዓ.ም. ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ስድስት ሚኒስትሮችን በመሾም እንደ ተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ የመንግሥት ሰራተኞች አስተዳደር ለማዘመን የነበረውን መዋቅር መለወጥ በማስፈለጉ በትዕዛዝ ቁጥር 23/54 “ጠቅላይ መስሪያ ቤት” የሚባል ተቋም (እንደተሻሻለው) በህግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 269/55 በይፋ ስራ ጀመረ፡፡ በዚሁ መጠሪያ እስከ 1967 ዓ.ም. ሲጠራ ከቆየ በኋላ ማዕክላዊነቱን እንደጠበቀ “የመንግሥት ሰራተኞችና መስሪያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን” በሚል በአዲስ ድርጅታዊ መዋቅር ተደራጅቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ከደርግ ውድቀትና የሥርዓት ለውጥ በኋላ የሽግግር መንግስቱ ሲመሠረት የማዕከልና የክልል አስፈፃሚ መ/ቤቶችን ሥልጣንና ኃላፊነት ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 41/88 የኮሚሽኑ ሥልጣንና ኃላፊነት በአዲስ መልክ ተደነገገ፡፡ ከሽግግር መንግሥቱ በኋላ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. አስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 256/94 ደግሞ “የሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ” በመባል ተጠሪነቱ ለአቅም ግንባታ ሚኒስትር ተደርጎ ተቋቋመ፡፡
በመቀጠልም በአዋጅ ቁጥር 691/2003 መሠረት የአቅም ግንባታ ሚኒስቴርና የሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ በመዋሃዳቸው “የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር” በሚል ስያሜ በ2003 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ስያሜውን እንደያዘ የተሰጡትን ተግባራትና ኃላፊነቶች እስከ 2008 ዓ.ም ሲወጣ ከቆየ በኋላ አገሪቷ በደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ልክ አገልግሎቱን በመንግስትና በግል ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ፣ የሰው ሀብት ልማትን፣ ተቋማዊ ለውጥን እና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማስተባበርና ለመከታተል እንዲያስችል በአዋጅ ቁጥር 916/2008 “የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር” ተብሎ እንደገና ተዋቀረ፡፡
ከዚህ መነሻ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ቢሮ የሲቪል ሰርቪስ ዘርፍን የሰው ሀብት ልማትና የሥራ አመራርን፣ የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማትን አቅም የመገንባት፣ የአገልግሎት አሰጣጥንና የቅሬታና አቤቱታ ሥርዓትን የመዘርጋት እና የሥራ አካባቢ ምቹነትን የማረጋገጥ፣ የማስተባበር እና የማስተግበር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በመቀጠልም በ2015 በጀት ዓመት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከቀድሞዉ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሪፎርም በመዉጣት ሲደራጅ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈጻሚ አካላትን
ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 199/2015 አንቀጽ 27 ከንዑስ አንቀጽ 1 እስከ ንዑስ አንቀጽ 16 ለፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሃብት ልማት ቢሮ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡