በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ ።
(ሆሳዕና፣ የካቲት/19/2018)
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ወደ ሪፎርም ዝግጅት ምዕራፍ ለሚገቡ ተቋማት አብይ እና ቴክኒክ ኮሚቴዎች በሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች ላይ በሆሳዕና ከተማ ውይይት አካሂዷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ውጤታማ የሪፎርም ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ እንዲሁም የፍኖተ ካርታ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ ተገብቷል።
በአገር ደረጃ የሪፎርም ስራዎችን በልዩ ትኩረት ከሚከናውንባቸው ሶስት ክልሎች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ መሆኑን የገለጹት አቶ ገብሬ፤ ስራው በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተመራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
የዝግጅት ምዕራፍ ዕቅዱ ለሪፎርሙ ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ሂደቱ በክልሉ የሚታየውን የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የተቋማትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች በስኬት ከተጠናቀቁና አስፈላጊው ምዘና ከተደረገ በኋላ ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባል ብለዋል።በመድረኩ ላይ በቀረቡ የፖሊሲ እና የዕቅድ ሰነዶች ዙሪያ ጥልቀት ያለው ውይይት ተካሂዶ የጋራ ግንዛቤ ተፈጥሯል።
የሪፎርም ስራው በክልሉ የሚታየውን የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና የተቋማትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የቢሮው የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።
የሪፎርም ዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን በስኬት ማከናወን ከቻሉ ከምዘና በኋላ ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ እና ፍኖተ ካርታ እና የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ የዕቅድ ሰነዶች ቀርበው ግንዛቤ ተፈጥሮባቸውል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ እና የቢሮው ምክትልና የተቋማት ለውጥ አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ይርዳ በቀጣይ ሊከናወኑ በሚገባቸው ተግባራት ላይ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
አብይና ቴክኒክ ኮሚቴዎቹም የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎችን በቁርጠኝነት ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ፣ የፋይናንስ ቢሮ እና የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ወደ ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ የሚገቡ ተቋማት መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር እንዳሻዉ ጣሰዉ(ዶ/ር) የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን በሆሳዕና ከተማ ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።