የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የተቋማት የአፈጻፀም ጥራት እና አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና ለማሻሻል በሪፎርም ስራዎች አመራር፣ በዜጎች ቻርተር፣ በተገልጋዮች እርካታ የዳሰሳ ጥናት እና በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ ለባለድርሻ አካላት በወልቂጤ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ይርዳው ስልጠና ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለፁት የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራታቸውን በማሻሻል ውጤታማ ተግባራት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የመንግስት ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት ግልጽ በሆነ መንገድ መስጠት እንዲችሉ የአመራሩና ባለሙያው አቅም መጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ የሚያስገኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም በተቋማት ውስጥ ይበልጥ ቀልጣፋና ውጤታማ አሰራርን ለመዘርጋት ዜጎች ቻርተር ዝግጅትና ትግበራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ህብረተሰቡ ከሚሰጡ አገልግሎቶች የሚያገኘውን እርካታ በሳይንሳዊ መንገድ ለመለካትና ክፍተቶችን ለመሙላት የሚረዳ ጥናት ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን አውስተዋል።
ተቋማት ተመሳሳይ የአፈፃፀም ደረጃ እንዲኖራቸው ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት አለበት ብለዋል።
በስልጠናው የክልል ተቋማት የሪፎርም ስራዎች ፎካል ፐርሰን፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ/ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎች ተገኝተዋል።