Skip to main content
00020

(ቡታጅራ፦ ሰኔ/20/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በዌቭ 2 ወደ መንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ለሚገቡ ግብርና፣ ገቢዎች፣ ፕላንና ልማት፣ እና ትምህርት ቢሮዎች የሪፎርም ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ እንደተናገሩት  እንደ ሀገር ሁሉንም የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ሪፎርሙ ለማስገባት ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው።

ቀደም ሲል የነበረው የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ለህብረተሰቡ ተገቢ እና ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት እየሰጠ ያልነበረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጠንካራ የተቋማት ግንባታ ለዘላቂ እድገትና ልማት ወሳኝ በመሆኑ በሁሉም ተቋማት ወጥ የሆነ ዕቅድ፣ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ መምሪያ እና ደንቦች እንዲኖር ይፈልጋል ብለው ተቋማት መረጃዎችን በተገቢ መልኩ  ማደራጀት ያስፈልጋል።

በሂደት ሁሉም የመንግስት ቢሮዎች ወደ መንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የሚገቡ መሆኑን የገለፁት አቶ ገብሬ ይህም ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ሲሉም ገልፀዋል።

የሪፎርሙ  ዋና ዓላማ ሀገራዊ ልማትንና ግቦችን የሚያሳካና የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚያረጋግጥ ተቋማትን መገንባት ነው ብለው ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት መስጠት፣መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

የሪፎርሙን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ የዝግጅት ምዕራፍ፣ የትግበራ ምዕራፍ እና የማጽናትና የፈጠራ ምዕራፎችን በቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትልና ተቋማዊ ለውጥና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ይርዳ በበኩላቸው በሀገር የተጀመረውን ሰው ተኮር አገልግሎቶችን የማላቅና  የተገልጋዩን የእርካታ ደረጀ ለማሳደግ ሰፊ ስራዎቾ እየተሰሩ ናቸው።

ስራ አካባቢን ምቹ በማድረግ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለው የአመለካከት እና የአስተሳሰብ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለው ተቋማቱ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ስራ እንዲገቡም አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት በዌቭ 2 ወደ መንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ውስጥ መግባት ለህዝቡ ቀልጣፋ እና ተደራሽ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ብሎም ከዘመኑ ጋር አብሮ ለመዘመን የሚረዳ ነው።

በቁርጠኝነት እና በቅንጅት መስራት ከተቻለ አይሳካም የሚባሉ ተግባራትን ማከናወን የሚቻል በመሆኑ ግንባር ቀደም ሆኖ በመምራት ለሪፎርሙ ውጤታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በእለቱም የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ፖሊሲ፣ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ፍኖተ_ ካርታ እና የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍን በሚመለከት የስልጠና ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።